አሮሞ፣ የሁለት ወገን ‹ጥሬ እቃ›? ———————- (መታወሻነቱ፣ ዚያድ ባሬ ለገደለው የኦነግ የመጀመሪያው ሊቀ-መንበር መገርሣ ባሪ)

አሮሞ፣ የሁለት ወገን ‹ጥሬ እቃ›?

———————-

(መታወሻነቱ፣ ዚያድ ባሬ ለገደለው የኦነግ የመጀመሪያው ሊቀ-መንበር መገርሣ ባሪ)

Daadhii D Gosa የተባለ ቄሮ፣ Oct. 10, 2017 በዚሁ መካነ ገፅ (FB) ላይ አስቸኳይ ማሳሰቢያ ልኮልኝ ነበር፡፡ ማሳሰቢያው “የኦሮሞ ጉዳይ እና የኢትዮጵያ ብያኔ፣ ከማሻሻያ፣ አመፃ እስከ አብዮት” የተባለው መፅሀፌ በተለይ ዛሬ ያለውን የኦሮሚያ እና የሱማሌ የድንበር ግጭት፣ ከሶስት አመታት በፊት የተነበየ በመሆኑ፣ እንዲሁም በእጅጉ መነበብ ያለበት አሁን በመሆኑ መታተም እንዳለበት የሚያሳስብ ነበር፤ የሚገርመው፣ በአማርኛ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ኦሮሞ ላይ አተኩሮ በዚያ መጠን መነበብ ህልም ነበር የሆነብኝ፤ 15,000 መፃህፍት ሰው እጅ ገብተዋል፤ በቅርቡ ብዙ የደከምንበት “ዲሞክራሲ” 2000 ታትሞ ገና አላለቀም፡፡

“የኦሮሞ ጉዳይ እና የኢትዮጵያ ብያኔ፣ ከማሻሻያ፣ አማፃ እስከ አብዮት” አሁን በአማርኛ ከማሳተም ይልቅ፣ በቻልኩት መጠን ሁሉ በሀሳብ አደርጅቼ በአፋን ኦሮሞ ቄሮ ጋ ለመድረስ ወስኜ እየሰራሁ ነው፤ ከጥቂት ወራት በኋላ እውን ይሆናል፡፡

ለዛሬው የሶስቱን ልሂቃን ግንኙነት እነሆ ቅምሻ፡-

ባህሩ ተፍላ፣ እ.ኤ.አ በ1987 ዓ.ም የአማራ (አማራ-ትግሬ by default) ገዢ መደብ የወል አስተሳሰብ የሆነውን አተያይ፣ እንዲህ ሲል በሁለተኛ ዲግሪው ማሟያ ጥናት አካቷል፡- “… ቁጥረ-ብዙው የኦሮሞ ሕዝብ በጋራ ከሚናገረው ቋንቋው በተረፈ እምብዛም የጋራ ማንነት የሌለው የትንንሽ መንግስታት ስብስብ ነው፤ እርስ በርስ ለመዋጋትም የማያመነታ ነው” (ባህሩ ተፍላ፣ 1987፡ 48)፡፡

በተለያዩ ምንጮች ውስጥ ኦሮሞ የሚገለፀው፣ እንደተበታተነ እና የሳሳ ስብስብ ከመሆኑም በላይ መሠረታዊ የብሔር ብያኔ መመዘኛዎች የሚያጥረው ተደርጎ ነው፡፡ ነገር ግን ከባህሩ በላይ ሙሉ ዘመኑን ለኦሮሞ ጥናት እየሰዋ ያለው መሀመድ ሀሰን (ፕ/ር)፣ ወደ ተለያዩ ግዛታዊ ቡድኖች ከመለያየቱ በፊት፣ ኦሮሞ የጋራ መንግስት እንደነበረው ብዙ የታሪክ ማስረጃዎችን በማቅረብ ያስረዳል (መሀመድ ሀሰን 1990፣ የኅዳግ ማስታወሻ 18) ፡፡

ኤርነስት ጊልነር በበኩሉ እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም “Nations and Nationalism” በሚለው ጥናቱ፣ “…የኦሮሞ ሕዝብ የዘውጌ ትሩፋት (ethnicity apple) የተነፈገ ቁጥረ ብዙው ዘረ-አዳም ሕዝብ ነው” በማለት ከመሀመድም በፊት ሀሳቡን አስተጋብቷል (Gillner 1983: 84) ፡፡

“ታላቋ ሶማሊያ”ን የመገንባት ህልም ይዘው የተነሱ የሶማሊያ ገዢ ልሂቃንም ኦሮሞን በተመለከተ ተመሳሳይ ሀሳብ ይጋሩ ነበር፤ ለመገንባት ለሚያልሟት“ታላቋ ሶማሊያ”፣ በብዙ ሚሊዮናት የሚቆጠረው የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ጥሬ ዕቃ ይታያቸው ነበር፡፡ የሚገርመው፣ ከአማራው ገዢ መደብ በበለጠ፣ ህልውናውን በመካድ ኦሮሞ፣ “ሶማሌ ሊደረግ የሚችል (somalized) ቅድመ-ዘውጌ (pre–ethnic) ጥሬ ዕቃ ነው” ብለው ያምኑ ነበር፡፡

ለዚሁ ዓላማቸው እንዲረዳ የጀኔራል ዚአድ ባሬ (እ.ኤ.አ ከ1969 – 1997 የሶማሊያን ገዥ) መንግስት፣ እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም “የሶማሊ አቦ ነፃነት ግንባርን /Somali Abo Liberation Front/” በማደራጀት የሀረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ እና ሲዳሞ ኦሮሞዎችን ሶማሌ ለማድረግ ፕሮግራም ቀረፀ፡፡ ይህ ኃይል የባሌ ገበሬዎችን አመፅ በመጥለፍ የተገኘ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ መሀመድ ሀሰን፣ እ.ኤ.አ በ1977 በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ማዕከል በተደረገ ስብሰባ ላይ፣ አንዱ የሶማሊያ ዲፕሎማት ይህንኑ ሀሳብ በሙሉ አቋም ሲገልፅለት የፖሊሲውን እውነትነት አረጓግጧል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከ14 ዓመታት በኋላ፣ መሀመድ በተመሳሳይ ቦታ አግኝቶ ያገኘው አንድ የህወሓት አመራርም የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የሚያይበት አግባብ ላለፉት 25 ዓመታትም ሆነ ዛሬ የኦጋዴን ልሂቃንን በመጠቀም የሚፈፅሙትን ለማድረግ እንደሚችሉ ከወዲያው ያሳብቅ ነበር፡፡፡

በተለይ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ በቃጣችው የ1969ኙ ወረራ፣ መጀመሪያ ላይ ባገኘችው ስኬት፤ ኦሮሞን አማራ አሊያም ሶማሊ ለመሆን የተዘጋጀ ቅርፅ አልባ ቅድመ-ዘውጌ (pre- Ethnic) ጥሬ ዕቃ እንደሆነ ያላትን እምነት በፅኑ አጠናከረች፡፡ ለዚህ ሀሳቧ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ያገለገለው ደግሞ ቀጣዩ ነው፡-

በጉልበት የሚጫንበትን የኢትዮጵያ ገዢ ቡድን እና እንወክለዋለን የሚሉት የባህል ቡድን (አማራ-ትግሬ) ማንነት ለመከላከል ሲሉ፣ ሀይማኖታቸውን የሚቀይሩ ኦሮሞዎች ተበራክተው ነበር፡፡ በተለይ የሀረር እና የባሌ ገበሬ፣ መሬቱ በነፍጠኛ እና አጃቢዎቹ ሰፋሪዎች ሲያዝበት፣ መሬቱን ቢያጣም ማንነቱን ለመከላከል እስልምናን እንደ መሸሸጊያ ተጠቅሞ ነበር፡፡ ይህ በዚህ ወቅት የሰፋው አግድሞሻዊ አንድነት በበኩሉ የሶማሌ ልሂቃንን አበረታታ፡፡

የአማራው ልሂቅ፣ የኦሮሞን ብሔራዊ ማንነትና አንድነት በክፉ አይን ማየቱ፣ የብሔርተኝነቱ ጡዘት ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት አደጋ ይሆናል ከሚል ስጋት በመነሳት ነው፡፡ የሶማሌ ልሂቃንም እንዲሁ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የሚቀጣጠል ከሆነ፣ የታላቋ ሶማሊያ ህልም ይጨናገፋል በሚል ድምዳሜ ነበር እንደ ትልቅ ጋሬጣ ያዩት የነበር፡፡ የኦሮሞ ነባር ድንበር እና የሚያልሟት ታላቋ ሶማሊያ ድንበር የሚዋዋጥ ነበርና፡፡

ሁለቱም ገዢ ልሂቃን፣ ከኦሮሞ ብሔርተኝነት በተቃራኒ ነበሩ:: ነገር ግን የስጋታቸው ምንጭ አንድ ዋነኛ ልዩነት ነበረው፡፡ የአማራ ልሂቃን ስጋት የሀገሪቷ የግዛት አንድነት መበተን ሲሆን፣ የሱማሊያ ልሂቃን ስጋት ደግሞ የ “ታላቋ ሶማሊያ” ህልም መጨናገፍ ነው፡፡ በተጨማሪም የመጀመሪያዎቹ ስጋት የመነጨው፣ የኦሮሞ ሀብት ካልታከለበት ኢትዮጰያዊ መንግስት ስለመፅናቱ በመጠራጠራቸው ሲሆን፣ ሱማሌዎቹ በበኩላቸው ኦሮሞን በተምኔታዊ (ideal) ካርታቸው ከላካተቱ (በገመቱት ደረጃ ካላገኙት) ታላቋ ሶማሊያ ቅዥት ብቻ ትሆናለች፡፡

ይህ ማለት የኦሮሞ ብሔርተኝነት ልደቱን ካከበረበት 1940/ 50ዎቹ ጀምሮ፣ የሁለት ወገን ውጫዊ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር ማለት ነው፡፡ ከሁለት ኃይሎች በኩል የመጣው ይኸ ተግዳሮት፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ከማዘግየቱም በላይ፣ አፍሪካ ውስጥ ከታየው ብሔርተኝነት በተለየ መልኩ የራሱን ልዩ መንገድ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር መጨመር አለበት፤ ቅዥ አገዛዝ የሚካሄደው በቴክኖሎጅና ማህበራዊ ዕድገት ከፍ ባሉ መንግስታት ነው፤ መስፍን ወልደ ማርያምም በደፈናው፣ የሳህለስላሴ ስርወ-ንግስና ኦሮሞን የያዘው በዚሁ ብልጫው ነው ከማለቱም በላይ ኦሮሞ ወደ ግዛተ-አፄው በመካተቱ ሀገርቷን በብዙ ነገሩ ወደ ድንቁርና ጎትቷታል ይላል፡፡

ነገር ግን ከአፍሪካ ሀገራት ብሄርተኝነት ጋር ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገው ሁለተኛው ገፊ ምክንያት፣ ከመስፍን በተቃራኒ ያስቀመጡ የዘርፉ ምሁራን ብዙ ናቸው፤ ለምሳሌ የፖል ባክስተር ብዕር እንደሚከተለው ተገልጧል፡-

“የኦሮሞ ብሔርተኝነት እስካሁን ከታዩት ይለያል፤ በዋናነት በኢትዮጵያ አገዛዝ ስር መያዝ፣ በምዕራባውያን ኃይላት ከመገዛት ስለሚለይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ሩቅ ከሆነ ሜትሮፖል የመጣ ሳይሆን እዚያው አገር የከተመ ነው፤ ገዢቹም ተወላጆች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ወይ የሰፋ የቴክኖሎጂ አሊያም የኑሮ ደረጃ የበላይነት አልነበራቸውም (BaXter 1994፡ 249)፡፡

ከሀገሪቷ ምሁራን መካከልም ሰፊ ማስራጃ በማቅረብ የሚከራከሩት እንደ ነጋሶ ጊዳዳ፣ መረራ ጉዲና፤ መሀመድ ሀሰን፣ አሰፋ ጃለታ፣ … መሳይ ከበደ (በከፊል) ያሉ ምሁራንም ኦሮሞን የመሰለ የተሻለ ማህበራዊ አቋም የነበረው የባህል ቡድን ወደ ግዛተ አፄው መጠቃለሉ የተለመደውን “የበላይ የበታቹን” የመያዝ ኃልዮት ያፈርሳል ሲሉ የባክስተርን ሀሳብ በጅጉ ያበለፅጉታል፡፡ የነበረውን የውጪ ኃያላን የዘመናዊ ጦር መሳሪያም እርዳታም በአሀዝ ያስቀምጣሉ፡፡

ከ1969 – 1970 ዓ.ም በነበረው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት፡-“የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባር” እና መደበኛ የሶማሊያ ወታደሮች በሀረርጌ፣ ባሌ እና ሲዳሞ የተወሰኑ የኦሮሞ ግዛት (ድንበር) ከመያዛቸው፣ ሰዎቹን ሶማሊ በማድረግ ሥራ ላይ ነበር የተጠመዱት፡፡ ይህ ማለት ታላቋ ሶማሊያን የመፍጠሩ ህልም፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ማንነትን ከመደምሰስ ሥራ ጋር የተዋደደ (የተጣመረ) ነበር ማለት ነው፡፡ “በዚህ ወቅት” ይላል መሀመድ ሀሰን፣ “የኦሮሞ ብሔርተኞች እንቅስቃሴ የሶማሊያ ወረራን ለመከላከል ሲሆን የአማራ ልሂቃን በበኩላቸው በኦሮሚያ ላይ የነበራቸው የቅኝ-ገዢነት ሚዛን (status quo) መጠበቅ ነበር”፡፡ ይህ ከሁለት አቅጣጫ መወጋቱ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዕድገትን በአስርታ (a decade) ሳያዘገየው እንዳልቀረም ይነገራል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ በ1910ሮቹ እና 1940ዎቹ መካከል እንዳበበው የአፍሪካውያን ብሔርተኝነት ሳይሆን ዘግይቶ በ1950ዎቹና ከዚያ በኋላ የተቀጣጠለ ነበር፡፡

የአማራና የሱማሌ ልሂቃን የኦሮሞን ብሔራዊ ማንነት ከማንቋሸሻቸው በተጨማሪ እንዲህ የሚል ማንነት እንደሌለም ተረት ፈጥረው ነበር፡፡ ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳየነው፣ በጋራ የሚጠየቀው የማንነት ጥያቄ እንደሌለ በስፋት ለማስረፅ ጥረዋል፡፡ ኦላና ዞጋ፣ በ1985 ዓ.ም በታተመው “ግዝትና ግዞት እና ሜጫና ቱለማ ማህበር” መፅሃፉ፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ማንነት ጥያቄ “ከኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩል የመታየት እና የመያዝ ጥያቄ” መሆኑን አብራርቷል (ኦላና ዞጋ፣ 1985: 75-7)፡፡ ከዚያም አልፎ የአፍሪካ ቀንድ ህዝብን እኩልነት ለማምጣት፣ ብዙ ስመ-ጥር የኦሮሞ ወጣቶች የህይወት መስዋእትነት ድረስ ከፍለዋል፡፡

ሌንጮ ለታ እንደሚለው ከደርግ መንግስት ባልተናነሰ፣ የኦሮሞን ወጣቶች የፈጀው ዚያድ ባሬ ነው ይላል፤ ኦነግ የያዘው የኦሮሚያ ካርታ፣ ከሚያልመው ጋር እንደሚዋዋጥ የተገነዘበው ዚያድ ባሬ፣ ጠለላ የሰጣቸውን የኦሮሞ ወጣቶች ገሚሱን አሳዶ ገሚሱን ፈጅቷል፤ የነጻነት ቀንዲሉ መገርሣ ባሪ ም ያኔ ነው የወደቀው፡፡

የሚገርመው ነገር ታዲያ፣ ብሔራዊ ማንነታቸው እና መብታቸው እንዲመለስላቸው እና እንዲታወቅላቸው ዛሬም ድረስ ነብስ ጭምር መገበራቸው ነው፡፡ ኤ ዲ ስሚዝ እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም፡-“The ethnic origins of Nations” ሲል ባሳተመው መፅሐፍ፣ “በሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት እንደሆነው ሁሉ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዛሬም ድረስ እያደገና እየተቀየረ የሚሄድ ነው፡፡ ቅርፁን የሚያገኘው የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ለመከላከል ከሚያደርገው ሂደት ነው፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ማለት ይቻላል፤ “የኦሮሞ ብሔርተኝነት በአንድ ወገን የአማራን የበላይነት ለመታገል፣ በሌላ ወገን የሶማሊያን ተስፋፊነት ለመገደብ የተፈጠረ ነው፡፡” በማለት የትግልና ተፅዕኖ የመቋቋም ውጤት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ዛሬም ከታች ከምናያቸው ሁለት ልዩነቶች ውጪ ያልተሻረ እውነታ መሆኑን በግሌ አምናለሁ፡፡

አሰፋ ጃለታ (ፕ/ር) በበኩሉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለኦሮሞ ትግል፣ ከሁለቱ በተጨማሪ ሉላዊነትም ሶስተኛ አንጓ (variable) በመሆኑ በደንብ ሊተኮርበት እንደሚገባ ያትታል፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ እኩልነት ላይ ያልተመሠረተው፣ የኢኮኖሚ መጥማጭነት ላይ የቆመው፣ የባህል ጫናን መሠረት ያደረገው እና የፖለቲካ የበላይነትን ያነበረው የአማራ አገዛዝም ሆነ የሶማሊያ ታላቅነት ህልም (ቅዠት)፣ ለሕዝባቸው አንዳች ጥሩ ነገር ይዞ እንደማይመጣ ያውቃሉ፡፡ መሀመድ ሀሰን፣ ክርስቲያን ኦሮሞ ብሔርተኞች፣ የኢትዮጵያን ገዢ ቡድን ክርስቲያናዊ ርዕዮተ-ዓለም እንቢኝ ሲሉ፣ ሙስሊም ኦሮሞ ብሔርተኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ የሶማሊያ ሀይማኖታዊ ፕሮፓጋንዳ ለመቀበል አንፈቅድም ወደ ማለት የዞሩት ከዚህ የተነሳ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ህወሓት ያንኑ የዚአድ ባሬ እሳቤ በተቀየደ መንገድ (controlled way) በመቀስቀስ ነው በኢትዮጵያ ሶማሌ ልሂቃን መሳሪያነት ለመጠቀም የሞከረችው፡፡ ኦሮሞ ዛሬም ልክ እንደ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ሁሉ ከሰሜን በትግሬ ልሂቃን በደቡብ ምስራቅ በሶማሌ ልሂቃን መንጋጋ ውስጥ እየታኘከ ነው፤ ከበፊቱ የሚለየው፣ ዛሬ በሁለቱም ወገን የሚደረገው ጫና የትግሬ ልሂቃን የሚቆሳቁሱት እና የሚቆጣጠሩት መሆኑ፣ እንዲሁም በደቡብ ምስራቅ መሳሪያ የሆኑት ልሂቃን በዋናነት ከኦሮሞ ጋር የመገፋት ታሪክ የሚጋሩት የኢትዮጵያ ሶማሌ (ኦጋዴኖች) መሆናቸው ነው፡፡

አብዲ ኢሌ ከነዚህ አጥፍቶ ጠፊዎች ጋር ተሰልፎ ዘላቂነት የሌለው ጥቅም ከሚፈልግ፣ ዘላቂ ሰላም ብቻ አዋጪ በሚሆንላቸው ሁለቱ ህዝቦች መካከል ጠባሳ ባይጥል ይመረጣል፡፡

Solomon Seyoum